የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መመረቅ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የሚያረጋግጥ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መመረቅ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የሚያረጋግጥ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መመረቅ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነውን ይህንን ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ በዛሬው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላይ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች ትላልቅ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ የሚችሉ ወደ 30 የሚጠጉ የአየር ማረፊያዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የአየር ማረፊያዎቹ ስርጭት ሀገራዊ አንድነትን እና ልማትን እኩል ለማስፈን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤በሰሜን 10፣ በምሥራቅ 5፣ በምዕራብ 7 እንዲሁም በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል አዲሱን የነገሌ ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ 6 የአየር ማረፊያዎች መኖራቸውን በዝርዝር አብራርተዋል።
የቦረና ሕዝብ የኦሮሞን ማንነት፣ባህልና እሴት ጠብቆ ያቆየ እንዲሁም ከጉጂና ባሌ ማኅበረሰቦች ጋር በትብብር የኖረ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሰላም ወዳዱ የቦረና እና ጉጂ ሕዝብ ልማት ብንዘገይም ደርሰንለታል ብለዋል።
አዲሱ የመሠረተ ልማት አውታር አካባቢው ከአዲስ አበባ ካለው የርቀት ስፋት አንጻር የሚፈጥረውን ተግዳሮት በመቅረፍ፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርፈ-ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባው ይህ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ እንደ ቦይንግ 737 ማክስ ያሉ ዘመናዊና ግዙፍ አውሮፕላኖችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
በሳምንት ሦስት የበረራ ቀናትን የሚያስተናግደው ይህ አየር ማረፊያ፤ የክልሎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከማነቃቃት ባለፈ የድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥንና የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ ታላቅ ራዕይ የሰነቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የአየር ማረፊያውን ለገነባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና የገበያ ትስስርን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ የአየር ማረፊያዎች ግንባታ በተለይም በደቡብና ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠንተው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
ለዚህም ስኬት ሰላም ወዳዱ የጉጂና የቦረና ሕዝብ የጀመረውን የልማት ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።