የአረፋ በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እያከበርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረፋ በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እያከበርን ነው
አዳማ/አምቦ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ )፡-የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እያከበርን ነው ሲሉ የአዳማ እና የአምቦ የእምነቱ ተከታዮች ተናገሩ።
1447ኛው የኢድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በአዳማ ከተማ የኢድ አደባባይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በድምቀት ተከብሯል።
የአዳማ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሙሐመድሁሴን አህመድ እንደገለፁት የኢድ አል-አድሃ በዓል በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ነው።
ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በሰላም፣ በፍቅርና አብሮነት ማሳለፍ እንዳለበት ተናግረው እርድ ሲከናወን አቅም ለሌላቸው በማካፈል ማክበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ የአካባቢውንና የሀገራቸውን ሰላም በአንድነት እንዲጠብቅ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን ነው ያሉት።
በአዳማ በተከበረው በዓል ላይ የተገኙት ሼህ ሸሪፍ ኢብራሂም በበኩላቸው የአረፋ በዓል በእስልምና ትልቅ ቦታ ያለው ታላቅ የአደባባይ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በበዓሉ ያለው የሌለውን እንዲያስታውስ ምስኪኖችና ድሆችን በማብላት ማሳለፍ አለበት ያሉት ሼህ ሸሪፍ ለቤታቸው ከሚያርዱት በማካፈል ከሌላቸው ድሆች ጋር አብረን የምናሳልፈው በዓል ነው ብለዋል።
የአረፋ በዓል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአደባባይ ወጥተው በአንድነት የሚያከብሩት ታላቅ በዓል መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሼህ ሱልጣን ቃሲም ናቸው።
በተክቢራና በሃይማኖታዊ ክንውኖች በመመራት በአደባባይ ወጥተን የምንሰግድበትና ፈጣሪያችንን የምናስታውስበትና የምናመሰግንበት በዓል ነው ብለዋል።
እርድ የሚፈጽሙ አካላት ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን በጋራ አብሮ ማሳለፍ አለባቸው ያሉት ሼህ ሱልጣን በመረዳዳትና በመተጋገዝ በአንድነትና በርህራሄ በዓሉን ማክበር አለብን ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በአምቦ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች የአረፋ በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እያከበሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ማዕድ በማጋራት መሆኑን ተናግረዋል።
የአምቦ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ አህመድ ስራጅ፣ የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት መከበሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የከተማው ሕዝበ ሙስሊም በዓሉን ለከተማዋ ዕድገት በጋራ በመትጋት ሊያከብረው ይገባል ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ የተገነቡ የልማት መሠረተ ልማቶችን በመንከባከብና ወደፊት ለሚከናወኑ ሥራዎችም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ አሚና ሹና የኢድ አል-አድሃ በዓል ሲከበር ቅራኔዎችን በማስወገድ፣ በአብሮነት፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ወጣት ሰፊዲን ሙሀመድ በዓሉን የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት ከቤተሰቦቹና ከጓደኞቹ ጋር በደስታ እያከበረ መሆኑን ተናግሯል።