ቀጥታ፡

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ያለንን በጎ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት የምናጠናክርበት በዓል ነው

ቦንጋ ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ያለንን በጎ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት የምናጠናክርበት በዓል ነው ሲሉ የቦንጋ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ አይደር ሁሴን ተናገሩ።

1447ኛው የዒድ አል-አድሐ (አረፋ) በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በቦንጋ ከተማ በድምቀት ተከብሯል ።

የአረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን የታዛዥነት፣ የመስዋዕትነት መገለጫ ሲሆን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት፣ የሰላምና የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ የሚጎላበት ነው።


 

የቦንጋ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ አይደር ሁሴን በወቅቱ እንደገለፁት፤ የአረፋ በዓል ለአላህ ያለንን ፍፁም ታዛዥነት የምናድስበት በዓል ነው።

በተጨማሪም የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ያለንን በጎ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት የምናጠናክርበት በዓል ነው ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገርና ለአካባቢው ሰላምና ልማት ያለው አስተዋፅኦና ተሳትፎውን የሚያጠናክርበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቶችም ከዚህ በዓል መልካም አርዓያነትን ሊማሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

በበዓሉ ላይ ተገኝተዉ መልዕክት ያስተላለፉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ በለውጡ መንግስት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሀገርና ለዞኑ ሰላምና ልማት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በሀይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት በመረዳዳትና በመተሳሳብ እንዲያከብሩም አሳስበዋል። 

የካፋ ዞን እስልምና ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ መሐመድ ጅብሪል የአረፋ በዓል በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርዓቶች የሚከበር የታዛዥነትና የመስዋዕትነት በዓል ነው ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት፣ የደከሙትን በማበርታት በአብሮነትና በፍቅር ሊያከብረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከእምነቱ ተከታዮች መካከል አቶ አንዋር ሀሰንና አቶ ከድር ሁሴን በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳትና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከበዓሉ አስተምህሮ ታዛዥነትንና የመልካምነት እሴትን በመላበስ በአንድነትና በአብሮነት በዓሉን ማክበር እንደሚገባ አንስተው በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የጤና እንዲሆንም ተመኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም