ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል ሲያከብር ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል ሲያከብር ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል ሊሆን ይገባል
ጋምቤላ፤ ግንቦት 19/ 2018 (ኢዜአ) ፡-ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል ሲያከብር ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል እስልምና ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ።
1 ሺህ 447ኛው የኢድ ዓል አድሃ (አረፋ) በዓል በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትኡስታዝ ሁሴን ካዩራ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር በመተዛዘን፣ በመደጋገፍና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል ሲያከብር ቤት ካፈራው አንድ ሶስተኛውን ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓል በእስልምና እምነት አስተምህሮ የታዛዥነትና የጽናት ተምሳሌት መሆኑን ጠቁመው ምዕመኑ እንደ እምነቱ አስተምህሮ በዓሉን ሊያከብር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ አብሮነቱንና አንድነቱን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ህዝበ ሙስሊሙ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ሀጅ ሀሰን ሙሀመድ በሰጡት አስተያየት የአረፋ በዓል በአንድነትና በአብሮነት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ቤት ካላቸው ላይ ለሌላቸው በማካፋል በዓሉን በአንድነትና በፍቅር እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአረፋ በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ፍቅርንና አንድነትን አጉልቶ የሚያሳይበት በዓል መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ኡስታዝ ሼህ በድሩ ጅማ ናቸው።
በመሆኑም በዓሉን አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች በመጠየቅና በመደገፍ እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።