ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ የእስልምና እምነት ትእዛዝ የሆነውን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ በዓሉን ሊያከብር ይገባል

ጅግጅጋ፣ ግንቦት 19 / 2018 (ኢዜአ)፡- ህዝበ ሙስሊሙ የእስልምና እምነት ትእዛዝ የሆነውን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ በዓሉን ሊያከብር ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ አህመድ መሀመድ ገለጹ።

የ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በጅግጅጋ ስታዲየም በተካሄደው የሶላት ስነ-ስርዓት ላይ በርካታ የከተማዋና የአካባቢው የእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዓሉን አስመልክቶ የሶማሌ ክልል እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ አህመድ መሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህዝበ ሙስሊሙ የእስልምና እምነት ትእዛዝ የሆነውን የተቸገሩ ወገኖችን የመደገፍ ተግባር ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢድ አል አድሃ በዓል ዋና መገለጫ መረዳዳትና ማካፈል መሆኑን ገልጸው፣ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ጠብቆ ማክበርና እርስ በርስ የመደጋገፍ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር የእምነቱ ትእዛዝ መፈጸም መሆኑን አስገንዝበዋል።

በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ህዝበ ሙስሊሙ በበዓል ወቅትም ሆነ ከበዓል ውጪ ባሉ ቀናት ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን የመደገፍና የመረዳዳት በጎ ባህሉን አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፥ የክልሉን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ህዝበ ሙስሊሙ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

በጅግጅጋ ስታዲየም በታላቅ ድምቀት የተካሄደው የ1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የሶላት ስነ-ስርዓት በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም