በዓሉ የተቸገሩትን የምንረዳበት፣አንድነታችንና አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ነው-በሐረር የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ የተቸገሩትን የምንረዳበት፣አንድነታችንና አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ነው-በሐረር የእምነቱ ተከታዮች
ሐረር፣ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የተቸገሩትን የምንረዳበት፣ አንድነታችንና አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ነው ሲሉ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ተናገሩ።
በሐረሪ ክልል የኢድ አል-አድሃ አረፋ በዓል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች እና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲዮም በታላቅ የሶላት ሥነ-ሥርዓት በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ቤት ያፈራውን ለተቸገሩ ወገኖች በማጋራት እናከብራለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምዕመናን አመልክተዋል።
በሶላት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኘችው ማወርዲ ሙህየዲን እንደተናገረችው፤ በዓሉን በመደጋገፍና በአብሮነት እናከብረዋለን ብላለች።
በተለይ በጎረቤትና በአካባቢው የሚገኙ የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በማስደሰት በዓሉን በጋራ እንደሚያሳልፉት ገልጻለች።
የእስልምና አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት የኢድ አል-አድሃ አረፋ በዓልን በመረዳዳትና በመተጋገዝ እናከብራለን ያለው ደግሞ አብዱላዚዝ አብዲ ነው።
እንደ ወጣት አብዱላዚዝ ገለጻ፤ እሱና ጓደኞቹ በአካባቢው የሚገኙ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ አቅመ ደካማ አረጋውያንና ሌሎችንም ወገኖች በማብላትና በመደገፍ በዓሉን ለማሳለፍ ተዘጋጅተዋል።
ሌላው የእምነቱ ተከታይ ሙስተርያ አደም በበኩሉ፤ በዓሉ ሁሉም በጋራ ተደስተው የሚያሳልፉበት በመሆኑ ከቤተሰብና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በአንድነት በደስታ እንደሚያሳልፉት ገልጿል።
የኢድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በማካፈልና በመደገፍ፣ አብሮነትን በማጠናከር የሚከበር በዓል ነው ያለው ደግሞ ወጣት ሁሴን አብዲ ነው፤ በዓሉንም የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስና በመረዳዳት እንደሚያሳልፈው ተናግሯል።