የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን መተሳሰብ እና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን መተሳሰብ እና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል
ባህርዳር ፤ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፡- የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን መተሳሰብ እና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ገለጹ።
1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በባህርዳር ከተማ ጋጃ መስክ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ሼህ መሃመድ ሰኢድ ባስተላለፉት መልዕክት የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ህዝበ ሙስሊሙ ሲያከብር እምነቱ በሚያዘው መሠረት ከሚፈጸመው እርድ አንድ ሦስተኛውን ለምስኪኖችና ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም በዓሉ ሰላምን የምናጸናበት፣ አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ የምናጠናክርበት እንዲሆን ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክት አስተላለፈዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ህዝበ ሙስሊሙ ሰላምን በመጠበቅ ልማቱ እንዲፋጠን እያደረገ ላለው እገዛ አመስግነዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብርም አብሮነትና አንድነቱ ይበልጥ በማጠናከር የጀመርነውን ሰላምን አጽንቶና ልማትን አጠናክሮ የማስቀጠል ጉዞውን ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባ በማስገንዘብ ነው።
በቀጣይ አምስት ዓመትም እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተማዋን ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ለማድረግ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ህዝበ ሙስሊሙ እንዲፈቱለት በየጊዜው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጀመረውን ሥራ ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የበዓሉ ታዳሚ ሼህ አደም ኢሳ እንዳሉት በዓሉን የምናከብረው እምነቱ በሚያዝዘው መሠረት የተቸገሩ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በማገዝ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በዕለቱ ከምናከናውነው እርድ እምነቱ በሚያዝዘው መሠረት ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ተደስተው እንዲውሉ በማድረግ ነው።
በዓልን የምናከብረው ካለን ላይ ለተቸገሩ ወገኖች ከማካፈል ባለፈ ሰላምን፣ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ነው ያሉት ደግሞ መምህር ከድር መሃመድ ናቸው።
እንዲሁም በዓሉን ከቤተሰቦቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላምና በደስታ ለማሳለፍ እንደተዘጋጁም ገልጸዋል።