የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ሲከበር ሰላምን በማፅናትና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ሲከበር ሰላምን በማፅናትና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል
ገንዳውሃ/ጎንደር/ ደብረ ብርሃን ፤ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ):- የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ሲከበር ሰላምን በማፅናትና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተመላከተ።
የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓል ሲከበር ሰላምን በማፅናትና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ በገንዳ ውሃ፣ በጎንደርና ደብረ ብርሃን ከተሞች ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች አመልክተዋል።
የገንዳውኃ ከተማ እስልምና የምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሙሀመድ ኑርዬ እንደገለጹት፣ የአረፋ በዓል የታላቁ ነቢይ ኢብራሂም የታዛዥነትና የመስዋዕትነት ታሪክ የሚዘከርበት ነው።
በዚህም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ስርአቱ በሚያዘው መሰረት እርስ በርስ የሚተሳሰቡበትና የአብሮነት እሴት የሚያጎለብቱበት መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።
ሌላኛው የሀይማኖቱ ተከታይ ሼህ ሙሀመድ ታደሰ በበኩላቸው፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖችን ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሀመድ በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የሚያሳየውን መደጋገፍና ወንድማማችነት በሌሎች ጊዜያትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ የኢድ አል አደሃ /አረፋ/ በዓል በጎንደር ከተማ በፋሲለደስ ስታዲዮም በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ተከብሯል፡፡
የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሀሰን ደሴ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት የአረፋ በአል የታዛዥነት የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ የሆነ ታላቅ በዓል ነው።
ይህን በዓል መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፋይዳውን በማጉላት የተቸገሩና አቅም የሌላቸው ወገኖችን በመደገፍ፣ ፍቅራችንና አብሮነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ማክበር አለብን ብለዋል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሰላም ለአብሮነትና ለጋራ ብልጽግና እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ለከተማዋ እድገት የሚያደርገውን አበርክቶ እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ሷልህ ሀሚድ እንዳለው በዓሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለው ለሌለው በማካፈል ማህበራዊና ሰብአዊ እሴቶቹን በተግባር የሚገልጥበት እለት መሆኑን ተናግሯል፡፡
አቶ መሀመድኑር ኡመር በበኩላቸው የአረፋ በዓል ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን መሰረት በማድረግ ታመው አልጋ ላይ የሚገኙ አንዲሁም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ የአረፋ በዓል ላይ የከተማዋ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዑስታዝ አህመድ መሐመድ አማን እንደገለጹት አስተዳደሩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የቦታና ሌሎች ጥያቄዎችን እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬውን በዓል ስናከብርም ጽናትንና መንፈሳዊ መታዘዝን የምንማርበትና አስተምህሮው በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ በዓልን ሲያከብር የመረዳዳትና የሰላም እሴቶችን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት።
የእምነቱ ተከታዮች ኑሩ መሀመድ (ዶ/ር) እና ወይዘሮ አይከል ሁሴን በዓሉ የአብሮነት እሴቶችን ጠብቀን፣ በመረዳዳት፣ ካለን ላይ ለሌለው አካፍለን የምናሳልፈው እለት ነው ብለዋል።