ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በመጠበቅ ለአብሮነት መጽናት እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በመጠበቅ ለአብሮነት መጽናት እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ ማጠናከር አለበት
ሚዛን አማን፣ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፡-ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በመጠበቅ ለአብሮነት መጽናት እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ ማጠናከር እንዳለበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ።
1ሺህ 447ኛ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሚዛን አማን ከተማ አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሸህ አደም መሐመድ እንዳሉት፣ የአረፋ በዓል እርስ በእርስ በመጠያየቅ የሚከበር በመሆኑ አብሮነት የሚጸናበት ነው።
በመሆኑም ለፈጣሪ በመታዘዝ ለመልካም ነገሮች መበርታት ከሕዝበ ሙስሊሙ ይጠበቃል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም መጽናት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ ዑመር ሙስጠፋ በበኩላቸው የእምነቱ ሥርዓት በሚያዘው መሠረት ተካፍሎ በመብላትና በመረዳዳት የአረፋን በዓል በጋራ ማሳለፍ አለብን ብለዋል።
በዓልን በአግባቡ ማክበር የሚቻለው ሰላምና ፍቅር ሲሰፍን በመሆኑ የመቻቻል ዕሴትን በማጠናከር ለአካባቢያችን ሰላም መጽናት ከመንግስት ጋር በትብብር በመስራት ልናጠናክር ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ሌዊ የአረፋ በዓል አብሮነትና መደጋገፍ ጎልቶ የሚታይበት በመሆኑ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራል ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙም ለከተማው ልማት እና እድገት ሲያደርገው የቆየውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት ለፈጣሪ በቅንነት መታዘዝና መገዛት አለብን ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እስማኤል ኑራ ናቸው።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኡስታዝ ሽኩር ጃፈር እና ወይዘሮ ጦይባ ተሬሳ በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው እና አቅም ከሌላቸው ወገኖች ጋር በጋራ እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌሎችን እንደ ራስ መውደድና ያለንን በማካፈል በዓልን በአብሮነት ማካፈል ሃይማኖታዊ ግዴታችን በመሆኑ ይሄን በመተግበር በዓሉን እያከበርን ነው ሲሉም አክለዋል።