ቀጥታ፡

በአረፋ በዓል የምናሳየውን ህብረትና አንድነትን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ መድገም ይገባናል - የእምነቱ ተከታዮች

አሶሳ፤ ግንቦት 19/2018(ኢዜአ)፦ በአረፋ በዓል የምናሳየውን ህብረትና አንድነትን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ መድገም ይገባናል ሲሉ የአሶሳ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተናገሩ።

1447ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአሶሳ ከተማ በኢድ ሶላት እና በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክንውኖች ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች የአረፋ በዓል የመረዳዳት እሴትን የሚያጎለብትና አብሮነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ምዕመናኑ አክለውም በአረፋ በዓል የምናሳየውን ህብረትና አንድነትን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ መድገም ይገባናል ብለዋል።


 

ከታዳሚዎቹ መካከል አሰይድ አብዱራሂም እና ዩሱራ እስማኤል እንደተናገሩት፤ የአረፋ በዓል ህዝበ መስሊሙ ያለውን በማካፈል የሚያሳልፈው በመሆኑ የመረዳዳት እሴትን የበለጠ የሚያጎለብት በዓል ነው።


 

የበዓሉን የሶላት ስነ-ስርዓት ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ጋር በጋራ ማክበራቸውን ጠቁመው፥ ይህን አንድነት በልማት  ስራዎች ላይም አጠናክሮ በመቀጠል ከህዝበ ሙስሊሙ የሚጠበቀውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላው የእምነቱ ተከታዮች ሙሐመድ እስማኤል እና አሚር ናስር በአረፋ በዓል የሚከናወነውን የእርድ ስነ-ስርዓት ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች በአንድነት እና በደስታ እንዲያሳልፉ ያደርጋል ብለዋል።


 

እሳቸውም ለበዓሉ በቂ ዝግጅት በማድረግ ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ሼህ ኢብራሂም ሲራጅ በበኩላቸው፤ የአረፋ በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ለአቅመ ደካማ ወገኖች እና ረዳት ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አለኝታነቱን የሚያሳይበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል።

በዓሉን አብሮነትን እና ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት እና ኃይማኖቱ በሚፈቅደው ልክ ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም