ቀጥታ፡

የኢድ አል አድሃ በዓልን በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ መንፈስ ማክበር ይገባል

ሀዋሳ ፤ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፡- ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመተጋገዘ መንፈስ ማክበር እንዳለበት የሀዋሳ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ሼህ ጀማል አብዱል ሸኩር አመለከቱ።

1ሺህ 447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ በስግደት ተከብሯል።

በወቅቱም የሀዋሳ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ሼህ ጀማል አብዱልሸኩር እንዳሉት፤ ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓልን ሲያከብር በመረዳዳትና በመተጋገዝ መንፈስ መሆን አለበት።


 

በዓሉ የመረዳዳትና የመተጋገዝ በዓል ነው ያሉት ሼህ ጀማል ረዳት፣ ደጋፊና አጋዥ የሌላቸውን አረጋውያን፣ ህጻናትና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በማገዝ ማክበር ይገባል ብለዋል።

ለበዓሉ ከሚከናወን ዕርድ አንድ ሶስተኛውን ለተቸገሩ ወገኖች አንድ ሶስተኛውን ለጎረቤት እንዲሰጥ የዕምነቱ አስተምህሮ ያዛል ያሉት ዋና ሰብሳቢው ይህን አስተምህሮ ተግባራዊ በማድረግ በዓሉን በፍቅር፣ በሰላምና በአብሮነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ዋና ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ሼህ ሙክታር ሙስጠፋ በበኩላቸው በዓሉ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት የሚሰበክበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓል ተረዳድቶ በደስታ የሚያከብረው በመሆኑ መላው የሀዋሳ ሙስሊም ማህበረሰብ በዕምነቱ አስተምህሮ መሰረት በዓሉን በመረዳዳትና በመተጋገዝ በሰላም እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።

 


አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ወይዘሮ አይሻ አህመድ እንዳሉት እስልምና እንደሚያዘው በዓሉን ረዳት ከሌላቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ ለማክበር ተዘጋጅተዋል።

ከዚህ ባለፈ በዙሪያችን ከሚገኙ የሁሉም ዕምነት ተከታዮች ጋር በመሆን በመጠያየቅና በመረዳዳት እናከብረዋለን ብለዋል።


 

ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ሀጂ ሀሺም ሁሴን በበኩላቸው በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን በጋራ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም