በዓሉ ያለው ለሌለው በማካፈል ሁሉም እኩል በደስታ የሚያሳልፈው ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ ያለው ለሌለው በማካፈል ሁሉም እኩል በደስታ የሚያሳልፈው ነው
መቱ/ጅማ ፤ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ) - የኢድ አል አድሃ (አረፋ) የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ያለው ለሌለው በማካፈል ሁሉም እኩል በደስታ የሚያሳልፈው በዓል ነው ሲሉ በመቱ እና ጅማ ከተሞች የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።
የዘንድሮው 1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የአደባባይ ሰላት ፕሮግራም በመቱ እና በጅማ ከተሞች በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።
በመቱ ከተማ በተካሄደው የበዓል ሥነ ሥርዓት ላይ የተሳተፉት አቶ ሚስባው ደጋጋ እንደገለጹት፤ በዓሉ ያለው ለሌለው በማካፈል ሁሉም እኩል በደስታ እንዲያሳልፍ የሚያዝ የእምነት መርሕ አለው።
እርሳቸውም ይህንን መሠረት በማድረግ ሌሎችን በመርዳት እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መሐመድጣሂር አባገሮ በበኩላቸው፣ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የመረዳዳትና የመደጋገፍ በዓል መሆኑን ጠቅሰው፣ በዓሉን ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ጭምር በአብሮነት እያሳለፉት እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የመቱ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ኤልያስ መሐመድ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአረፋ በዓል የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶቻችንን ይበልጥ አጠናክረን የምናስቀጥልበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞቻችን ጋር በአብሮነት እና በወንድማማችነት በማክበር የበዓሉን እሴት ማጎልበት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጅማ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ የከተማው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼክ መሀመድ አሚን ተማም፤ ሀገር ሰላምና እድገቷ ቀጣይነት የሚኖረው ስለ ሰላም በተግባር ስንሰራ በመሆኑ፣ ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ማስቀደም ይኖርብናል ብለዋል።
የበዓሉ ታላቅ መልዕክት ሰላምና መተሳሰብ በመሆኑ፣ አቅመ ደካሞችን በመርዳትና አንዱ ሌላውን በመምከር ለሀገር አንድነት ዘወትር መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የጅማ ከተማ የበዓሉ ታዳሚ ሀሊማ አብዱልባሲጥ በበኩሏ የሀገር ማደግ በመተሳሰብና በማካፈልም ጭምር ነው ብላለች። ይህ ደግሞ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በቀጣይነትም ሊደረግ ይገባል ስትልም አስገንዝባለች።
በተግባር ለሀገር መስራት ማለት በየትኛውም ጊዜ ሰላምን ማስቀደም ነው ያሉት ደግሞ አቶ አብዶ ከማል እና አዩብ አብዱልከሪም ናቸው።
ዘወትር ለሰላምና ለመልካም ነገር በመትጋት ሀገርን መቀየር እንደሚቻል የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከበዓሉ ቀደም ብለው ለአቅመ ደካሞች የሚሆን ድጋፍ ሲያሰባስቡና ሲያዘጋጁ እንደነበርና ይህንንም በጎ ተግባር ከበዓሉ በኋላም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።