ቀጥታ፡

ትምህርት ለትውልድ

ቴክኖሎጂ በረቀቀበት በዚህ ዘመን ያለ ትምህርት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል በመገንዘብ  መንግስት ዘርፉን የማኀበረሰብ የወል ትርክት መፍጠሪያና የሀገር ዘላቂ ዕድገት ማስቀጠያ ድልድይ አድርጎ ወስዶታል። መንግሥት ሁለንተናዊ ብቃት ያላቸውን ዜጎች በማፍራት የሀገሪቱን የነገ ተስፋ ለማለም ትምህርትን እንደ ቁልፍ መሣሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል።

በዚህም መሠረት ላለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ የታዩ ስብራቶችን ለመጠገን ሰፊ የለውጥ መርሃ ግብሮች ተተግብረዋል። 28 ዓመታት የቆየውን ፖሊሲ በመቀየር፣ አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ ወደ ትግበራ እንዲገባ ተደርጓል። ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅና የብቃት ማእቀፍ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል።

ባለፉት ዓመታት ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል "ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄን በመፍጠር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የመሠረተ ልማት ግንባታን የማፋጠን ሥራ ተጠቃሽ ነው። በተለይም ዓለም አቀፍ አድናቆት ያተረፈው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር፣ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ወደ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲያድግ ተደርጓል። ይህ ተግባር የተማሪዎችን ትምህርት የማቋረጥ ምጣኔ ከመቀነሱም በላይ ለወላጆች ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል።

በዲጂታል ዘርፍም "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" አጀንዳን መሠረት በማድረግ የዲጂታል ትምህርት ስትራቴጂ ተቀርጾ በርካታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኮምፒውተር ላብራቶሪና በኢንተርኔት እንዲገናኙ ተደርጓል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጥራት ለማረጋገጥም ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮ እንዲለዩና ወደ ራስ-ገዝነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል። የመውጫ ምዘና (Exit Exam) ተግባራዊ መደረጉም የተመራቂዎችን ብቃት ለማረጋገጥ የተወሰደ ቁልፍ እርምጃ ነው።

መንግሥት ትምህርትን ከንድፈ ሐሳብ ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር ሀገር በቀል ዕውቀትን በሥርዓተ-ትምህርቱ ውስጥ አካቷል። ባለፉት አምስት ዓመታት 34 ሺህ በላይ የመዋዕለ ሕፃናት ግንባታዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ተሳትፎን 36.7% ወደ 59.8% ማሳደግ ተችሏል። በተጨማሪም 17,500 በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና 38 ሺህ በላይ ተጨማሪ ክፍሎች ተገንብተዋል። በትምህርት ተደራሽነት ረገድ አሁን ላይ 27 ሚሊዮን የሚጠጉ የአጠቃላይ ትምህርትና 828 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

በቀጣይ  ዓመታት የቅድመ-አንደኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን 100% ለማድረስ ታልሟል። የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ቁጥር ወደ 2,150 ለማሳደግና የተማሪ-ክፍል ጥምርታን በአንደኛ ደረጃ 1 50 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 1 40 ለማድረግ በትኩረት ይሠራል። የወደፊቱ ትኩረት "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ላይ በማድረግ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለማስፋፋት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም