ቀጥታ፡

በምሥራቅ ቦረና ዞን እየታየ ያለው የግብርና ትራንስፎርሜሽን፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ማረጋገጫ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦በምሥራቅ ቦረና ዞን እየታየ ያለው የግብርና ትራንስፎርሜሽን፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዚህ ወቅት ብቻ ታታሪ አርሶአደሮች ከ176,223 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ላይ እንደሚገኙና ከዚህም ከ3.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።


 

ይህ የእርሻ ልማት ሥራ ከ101,000 በላይ አባወራዎችንና እማወራዎችን በማሳተፍ እንዲሁም ዘመናዊ ትራክተሮችን በመጠቀም እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተደራጀ የክላስተር እርሻ አማካኝነት እምቅ አቅማችንን ወደ ምርታማነት እየቀየርን እንገኛለን ብለዋል።


 

በምሥራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ ከሚገኙት ሰፋፊ የስንዴ ክላስተሮች ጀምሮ እስከ ዋና ዋናዎቹ የጤፍ፣ የበቆሎ እና የቦሎቄ ምርቶች ድረስ እየታዬ ያለው ውጤት፤ የሀገር ውስጥ የምግብ አቅርቦታችንን የማረጋገጥ ጉዞ ላይ ለመገኘታችን ህያው ምስክር መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም