ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት ፈተና በማውጣት ሕዝቡን በቁርጠኝነት የሚያገለግል አሻጋሪ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት ፈተና በማውጣት ሕዝቡን በቁርጠኝነት የሚያገለግል አሻጋሪ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አሳይቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት ፈተና በማውጣት ሕዝቡን በቁርጠኝነት የሚያገለግል አሻጋሪ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ሲሉ የአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ተንቀሳቃሽ ትዕይንተ ልማት እንዲሁም ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የጎንደር ከተማ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ዕጩዎች፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፤ የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር)፣ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ ዘላለም ልጃለም (ዶ/ር) እና ሌሎች ታድመዋል።
አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ ሀገራዊና ቀጣናዊ ፈተናዎችን በመሻገር ኢትዮጵያን የብልፅግና ማዕከል እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።
በመስኖ ስንዴ ልማት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት በማስመዝገብ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የአጼ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት በአስደናቂ ሁኔታ በማደስ የኢትዮጵያን ብልፅግና ትንሳኤ እያበሰረ ነው ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝነትና በፅናት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ሕዝቡን በትጋትና በቅንነት ለማገልገል የተጓዘው ርቀት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጀመረውን ልማትና ዕድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ መሆኑን በማንሳትም የጎንደር ህዝብ ለሰላምና ለፍትህ ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ዜጎች ለብልፅግና ድምጽ በመስጠት የተጀመረውን ልማት እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።