ብልጽግና ፓርቲ በአካታች ፖለቲካና በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ በአካታች ፖለቲካና በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል
ቦንጋ ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በአካታች ፖለቲካና በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን በማስመልከት ክልል አቀፍ የማጠቃለያ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ድጋፍ ሰልፍ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በሰልፉ ባስተላለፉት መልዕክት ፓርቲው በአካታች ፖለቲካና በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ ተግባር አከናውኗል።
ፓርቲው አዳዲስና አሻጋሪ ሀሳቦችን በማፍለቅ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተስማሚ የሆነ ስነ-ምህዳር መፍጠሩን አንስተው የህዝብ የቆየ የልማት ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በብልጽግና ፓርቲ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሀገራችን ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መመረቃቸው፣ የክልሉ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ተጠብቆ ከቱሪዝም መዳረሻ ልማት ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎች የፓርቲው ህያው አሻራዎች መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳደሩ አመልክተዋል።
በለውጡ መንግሥት በየደረጃው የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስቻሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ ሰላምን የማስፈን ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፓርቲው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የህዝቦች የዴሞክራሲ፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።
ፓርቲው የዘመናት ጥያቄ የነበረውን በክልል የመደራጀት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የክልሉን ህዝብ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መመለስ ችሏል ብለዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው ፓርቲው ለዘመናት የተከማቹ የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን በመመለስ በርካታ ድሎችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ፓርቲው በዞኑ በለውጥ ዓመታቱ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካውና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች በርካታ ውጤቶች ማዝመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህም ከለውጡ በፊት ቃል የተገቡና ተጀምረው የተስተጓጎሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቁመዋል።
ፓርቲው የጀመራቸው ስራዎችና ያስመዘገባቸው ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ብልጽግናን መምረጥ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የሰልፉ ታዳሚ የሆኑት የታርጫ ከተማና የካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ነዋሪዎች አቶ ተረፈ ዴቫንቾ እና ወይዘሮ ዘላላም አስፋው ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ሁሉን በእኩልነት ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ድሎችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህም የማይደፈሩ የሚመስሉ ውጤቶችን በመሠረተ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።