ቀጥታ፡

በክልሉ ሰላምን በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቅንጅት ማሳካት ተችሏል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ደሴ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቅንጅት ማሳካት መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በምረቃው ወቅት እንደገለፁት፤ የክልሉን ሰላም በማጽናት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለውጤት እንዲበቁ ተደርጓል።


 

የልማት ፕሮጀክቶቹን በቅንጅት በማሳካት የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ፣ የገበያ መረጋጋትን ለማምጣት፣ የስራ እድልን ለመፍጠር፣ የትምህርትና የጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የክልሉን እድገት በማረጋገጥ ወደ ሁለተናዊ ብልጽግና የማሸጋገር ተግባራት በቅንጅት እንደሚከናወኑ ጠቁመው በደሴ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የአስፋልት መንገድና ሌሎች የመሰረት ልማት ግንባታዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው የከተማውን ሰላምና ልማት ዘላቂ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በዚህም በከተማው የአስፋልት መንገድ፣ የኮሪደር ልማት፣ የመናኸሪያ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የትምህርት ቤት ማስፋፊያና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠናቅቀው ዛሬ ለምርቃ በቅተዋል ብለዋል።

የልማት ስራዎቹ መንግስት ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በሰጠው ትኩረት የተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትም አሳድገዋል ነው ያሉት።

በምረቃ መርሃ ግብሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም