የዒድ አል አድሃ በዓልን በአብሮነት ለማክበር ተዘጋጅተናል -በሚዛን አማን ከተማ የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አል አድሃ በዓልን በአብሮነት ለማክበር ተዘጋጅተናል -በሚዛን አማን ከተማ የእምነቱ ተከታዮች
ሚዛን አማን፣ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፡-1ሺህ 447ኛ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በአብሮነት ለማክበር መዘጋጀታቸውን በሚዛን አማን ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።
ለፈጣሪ በጥልቅ እምነት መታዘዝን የሚያሳየው የአረፋ በዓልን በአብሮነት ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የበዓል ዝግጅቱን በማስመልከት ኢዜአ በሚዛን አማን ከተማ ካነጋገራቸው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች መካከል አቶ ሰይድ ይመር እንዳሉት፣ እምነቱ በሚያዘው መሰረት የአረፋ በዓልን አቅመ ደካሞችን በማገዝ ለማክበር ተዘጋጅተዋል።
በአካባቢያቸው ላሉ አቅመ ደካሞች ለበዓል መዋያ ካላቸው ላይ በማካፈል የጋራ ደስታን ፈጥረው እንደሚያሳልፉም ገልጸዋል።
ለበዓሉ በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት በገበያው በመኖሩ አቅማቸው በፈቀደው መጠን ገዝተው እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሸምስያ ከድር የዘንድሮ የአረፋ በዓል ገበያ የተረጋጋና ምርትም በበቂ ሁኔታ የቀረበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግብርናም ሆነ የፋብሪካ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በዓሉን በደስታና አቅመደካሞችን ጭምር በመደገፍ ለማክበር እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል።
በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ፣ ከጎረቤትና ከአቅመ ደካሞች ጋር ሲከበር ከፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያሰጣል ያሉት ደግሞ አቶ አብዱ ባርጊቾ ናቸው።
ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ካለን ማካፈል ሃይማኖታችን የሚያዘው ግዴታችን በመሆኑ የተሻለ ዝግጅት አድርገን የበዓሉን ቀን በአብሮነትና በደስታ ለማክበር እየተጠባበቅን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ፋጡማ አባገሮ የተባሉ ሌላዋ የእምነቱ ተከታይ በበኩላቸው ከጥንት ጀምሮ የመጣውን የአብሮነት እሴት ጠብቀው በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ጭምር በጋራ እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።