ቀጥታ፡

የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን እርስ በእርስ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18 /2018 (ኢዜአ)፡-ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን እርስ በእርስ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ  በአብሮነት ማሳለፍ እንደሚገባ  የሃይማኖት አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የእርድ በዓል የሆነው ዒድ አል-አድሃ (አረፋ) መሆኑ ይታወቃል።

በነገው እለት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን 1ሺህ447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በማስመልከት ኢዜአ ከሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ጋር ቆይታ አድርጓል። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሃጂ ሰሂድ አህመድ እንደገለጹት ፤የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን የእርስ በእርስ ግንኝነቶችን የሚጠናከሩበት እና የተቸገሩ ወገኖች የሚረዱበት ታላቅ በዓል ነው።

ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት እና የአብሮነት እሴቶችን ለማስቀጠል በዓላት ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም በነገው እለት የሚከበረው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ከአቅመ ደካሞችና ከጎረቤቶቻቸው  ጋር በአንድነት ለማክበር  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ሌላኛው የሃይማኖት አባት ሼህ አብዱልመናን ሁሴን፤ በዓሉ የመስዋትነት እና የመሰጠት ምሳሌ በመሆኑ ሁሉም በአንድነት በእኩል ስሜት በድምቀት እንደሚያከብረው አስታውቀዋል።


 

የእምነቱ ተከታይ የሆኑት አቶ ከድር ብላታ እና አሊድ ሰሂድ እንደገለጹት፤ በዓላቶች ሁሉ አብሮነትን የሚያጠናክሩ የመረዳዳት መንፈስ ጎልቶ የሚታይባቸው ናቸው።


 

የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ እና ጎረቤቶች በጋራ ሆነው በአንድነትና በመተሳሰብ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም