ቀጥታ፡

በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ ተቋማት በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲደራጁ እየተደረገ ነው

አምቦ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የመንግስት አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ ተቋማት በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።

በአምቦ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ፕሮጀክቶች ምረቃና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በገባው ቃል መሰረት በርካታ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በብዛት ገንብቶ ለአገልግሎት እያበቃ ይገኛል።

በዚህም መሰረት በአምቦ ከተማ አስተዳደር ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ አድርጓል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የአምቦ ከተማ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ለተለያዩ ቢሮዎች አገልግሎት የሚውል ባለ አምስት ወለል ህንፃ፣ በርካታ ሼዶችና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎች ተጠናቀው ተመርቀዋል።

በወቅቱም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ እንደገለፁት፤ በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ተቋማት በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እየተደራጁ ይገኛሉ ብለዋል።

ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ የማይተካ ድርሻ አለው ነው ያሉት።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት ህብረተሰቡ ጊዜና ጉልበቱን በልማት ላይ እንዲያውል ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።

እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎትን ከአድሎ የጸዳና ጥራት ያለው በማድረግ ብልሹ አሰራርን በማስወገድ በኩል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው፤ መንግሥት ከተሞችን ለኑሮና ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።

የአምቦ ከተማን የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ የወንጪ-ዳንዲ-ኢኮቱሪዝም መንደር እና ሎጅ እንዲሁም ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃጫሉ ገመቹ ናቸው፡፡


 

ዛሬ በከተማው ከተመረቀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተጨማሪ ሼዶች፣ የከተማ ኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉም ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም