ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ተፈትኖ የመሻገር፣ የመታዘዝ እና የመሥዋዕትነት በዓል ነው። ነቢዩ ኢብራሂም በአላህ ትእዛዝ ልጃቸውን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጁበት፤ ጽናታቸው ተፈትኖም ያሸነፉበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ስናከብር ቅንነትን፣ መልካምነትን፣ መታዘዝን፣ በጎ አድራጊነትንና ትኅትናን በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በተመሳሳይ መልኩ ሀገር የምትጸናው በመሥዋዕትነትና በትውልድ ቅብብሎሽ በሚከፈል ዋጋ መሆኑን በመገንዘብ ለምንወዳት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከልብ በሆነ ፍቅር አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል ማጽናት እና ማሻገር ከሁላችንም ይጠበቃል ።
በዓሉ በሀገራዊ ምርጫ መዳረሻ የሚከበር ነው። መላው ሕዝበ ሙስሊም በመጪው ምርጫ በመሳተፋ ሀገረ መንግሥት የማጽናት ታሪኩን እንዲያስቀጥል አደራ እላለሁ ብለዋል።