ቀጥታ፡

የላፍቶ ሆስፒታል የካንሰር እና የልብ ህክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ያድናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18 /2018 (ኢዜአ)፡- የላፍቶ ሆስፒታል የካንሰር እና የልብ ህክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት የሀገርን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያድን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ የተደገፈው እጅግ ዘመናዊው የላፍቶ ሆስፒታል፤ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ግዙፍ የህክምና ማዕከል በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ፣ 17 ዘመናዊ ህንፃዎችን ያቀፈ እና 500 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ያለው ነው ብለዋል።


 

ሆስፒታሉ የካንሰር እና የልብ ህክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት ዜጎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀርና የሀገርን የውጭ ምንዛሬ የሚያድን መሆኑንም አብራርተዋል።

የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ልዩ የሚያደርገው በ(AI) የሚደገፉ እጅግ የረቀቁ መሣሪያዎች ያሉት ነው ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የ2026 ምርት PET-SCAN እና የሂሊየም ትነትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር MRI- 3 Tesla ማሽኖች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ልብ አንድ ጊዜ መትታ ሳትጨርስ ሙሉ ምርመራ ማድረግ የሚችል CT Scan 640 Slice እና በቀጭን የደም ሥር በመግባት የልብና የአንጎል ችግሮችን የሚያክም የልብና የደም ሥር ላቦራቶሪ (Cath Lab) መሟላቱን ከንቲባዋ አመልክተዋል።

የጡት ካንሰርን በቅድሚያ ለመመርመር የሚያስችል Mammography (3D) እና ሙሉ በሙሉ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ የሆነ Robotic Laboratory (TLA) በውስጡ ይዟል።

ዘመናዊ የአልትራሳውንድ፣ ዲጂታል ኤክስሬይ (X-Ray) እና በሰዓት 80 ሜትር ኩብ ኦክስጂን የማምረት አቅም ያለው የሜዲካል ጋዝ ማምረቻ ፕላንት መሟላቱንም አክለዋል።

የኢንፌክሽን ችግርን ለማስቀረት የሆስፒታሉ ግድግዳዎችና ወለሎች ባክቴሪያን ሙሉ በሙሉ በሚከላከል (Anti-bacterial) ቁስ የተገነቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የራሱ የውኃ ጉድጓድ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕላንት እና 18 ዘመናዊ የአስከሬን ማቀዝቀዣዎችን ማካተቱንም አመልክተዋል።

የዚህ ሆስፒታል ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን ለለፉ አመራሮችና ለመላው የአካባቢው ማህበረሰብ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም