ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ለማዋል በምርምር የማስደገፍ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ለማዋል በምርምር የማስደገፍ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሀዋሳ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ለማዋል በምርምር የማስደገፍ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመላክቷል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ “የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ሥርዓቶችን ለሰላም፣ ለአስተዳደር፣ ለፍትህ እና ለዘላቂ ልማት እንደገና ማዕከላዊ ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ ኢትዮጵያ ያሏት ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለልማትና ሰላም ግንባታ የሚኖራቸው ፋይዳ በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።
በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ ሀገር በቀል ዕውቀትን እንደገና ማዕከላዊ ማድረግ ከኦሮሞ ገዳ ሥርዓት አንጻር ለሥነ ምግባር፣ ለዴሞክራሲ፣ ለግጭት አፈታት እና ለማህበራዊ አስተዳደር የሚኖረውን ሚና በተመለከተ ጽሁፍ ቀርቧል።
ጽሁፉን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አለሙ ሀይሉ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የላቀ ሚና አላቸው።
ለአብነትም የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ለኢኮኖሚ፣ ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ልማትና አስተዳደር ያለውን የላቀ ሚና አንስተው ዕሴቱ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የበኩሉን እንዲወጣ ለማስቻል በጥናት ተደግፎ በሥርዓተ ትምህርት እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል።
በሀገር በቀል ዕሴት ትውልድን በሀገራዊ የሥነ ምግባር መርሆ እና ዕሳቤ በማነጽ ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ለማጽናት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ጅምር ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የጌዴኦ ሀገር በቀል የመሬት ጥበቃና ልየታ ሥርዓትን በተመለከተ ጽሁፍ ያቀረቡት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሀገር በቀል ትምህርት ጥናት የጌዴኡፋ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር ደሳለኝ በቀለ ናቸው።
በሀገሪቱ ያለው ነባር እሴቶች የማህበረሰብን የውስጥ ዕውቀት የሚያበረታቱና ዘመናዊ ትምህርት ከመምጣቱ አስቀድሞ የነበሩ በመሆናቸው ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
የጌዴኦ ማህበረሰብ ለዕጽዋት ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረት ከሁሉ ከፍ ያለ መሆኑን አንስተው ይህም ለስነ ህይወት የሚሰጠውን እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያሳይ አስረድተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ጥናት ተቋም ተጠባባቂ ዳይሬክተር አበራ አርጎ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ የሲዳማ ዕሴቶችን በምርምር አስደግፎ መሰነድ፣ መጠበቅና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግን ግቡ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ሻፌታ፣ ጋሻ፣ ጦርና ሌሎች የተለያዩ ባህላዊ የመገልገያ ቁሳቁስና በተለያየ መልኩ የተጻፉ ታሪኮችን የመሰብሰብና በአንድ ስፍራ በተደራጀ መልኩ የማስቀመጥ እና የሲዳሙ አፎ መዝገበ ቃላት ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉን አስረድተዋል።
የሲዳማ የዘመን አቆጣጠር፣ የመንግስት አስተዳደር ሉዋ፣ የግጭት አፈታት አፊኒ እንዲሁም ከግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው በዓለም አቀፍ ጆርናሎች እንዲታተሙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲሁም የዜጎችን አብሮነትና ትስስር አጠናክረው ያቆዩ ዕምቅ ዕሴቶች የታደለች ሀገር ናት ያሉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፊጮ ናቸው።
እነዚህ ሀብቶች በሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት ተደግፈው ለሀገሪቱ አሁናዊ ጥያቄዎች ቁልፍ መፍቻ መንገድ እንዲሆኑ የመሰነድ፣ የማስተዋወቅና ግንዛቤና ልምዶችን ለማካፈልና ለማሳደግ በሚያግዙ ውይይቶችን የማመቻቸት ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ታፈሰ ማቴዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከውጭ ከተቀዱ ሀሳቦች ይልቅ ሀገር በቀል ዕሴቶችን መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሀገር በቀል ዕሴቶችን በምርምር አስደግፎ የመሰነድና ለትውልድ ማሸጋገር አለፍ ሲልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።