የላፍቶ ሆስፒታል ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተሰነቀው ርዕይ ትልቅ ማሳያ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የላፍቶ ሆስፒታል ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተሰነቀው ርዕይ ትልቅ ማሳያ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ የላፍቶ ሆስፒታል ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተሰነቀው ርዕይ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ዘመናዊውና ግዙፉ የላፍቶ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት በይፋ መመረቁን ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ መመረቅ ኢትዮጵያን ቀዳሚ የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተሰነቀው ብሔራዊ ርዕይ ትልቅ ማሳያና አሻጋሪ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ ሆስፒታሉ በኢትዮጵያ የተሻሻለውን የመከላከል እና አክሞ የማዳን የሕክምና ፖሊሲ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስና መሰል የረቀቁ የዘርፉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታን ለማስቀጠል ለተያዘው ግብ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ይህ እጅግ ዘመናዊና ግዙፍ የሕክምና ተቋም እንደ ካንሰር፣ ውስብስብ የልብ ሕመም እና ተያያዥ የሕክምና ሁኔታዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ አቅሞች የተገነቡበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች እዚሁ ሀገራቸው ውስጥ ልዩ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።
ይህ ታላቅ ተቋም የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀየር ባለፈ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ራሷን ለመቻልና ለሀገራዊ ልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሕያው ምስክር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።