የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል - ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል - ሸማቾች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በየአካባቢው መስፋፋታቸው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግና ገበያን በማረጋጋት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያችን በመጀመሩ የግብይት ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ምቹ አድርጎታል።
አስተያየት ከሰጡ ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ገነት አድማሱ፤ ገበያው በአቅራቢያችን በመከፈቱ የፍጆታ እቃዎችን በቀላሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አስችሎናል ብለዋል።
ይህ አይነት ገበያ መኖሩ ለነዋሪዎች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎትን ከማግኘት ባለፈ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ትልቅ አስታዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ጸጋ አዱሽ በበኩላቸው፤ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የአትክልትና ፍራፍሬ በብዛት ከመቅረቡ ባሻገር ሰፊ አማራጮች የሚገኙበት ነው ብለዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በየአካባቢው መኖሩ ለአቅመ ደካሞችና ረጅም መንገድ ተጉዘው መገበያየት ለማይችሉ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልጸው፤ ገበያው ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያገኝ የገለጸችው ደግሞ ማአዛነሽ መለሰ ናቸው።
በቅዳሜ እሁድ ገበያዎች ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከል እየሩሳሌም ሐብቶም፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ነዋሪዎች ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ይህን ፍላጎት ለማሟላት ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ሌላኛዋ ነጋዴ ቤተልሔም አዱኛ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የዋጋ ንረትን በመቀነስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት መጀመሩን ገልጸው፤ ከመደበኛ ሱቆች ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ሸማቾች በቀላሉ በአቅራቢያቸው መገብየት የሚያስችሉ በሁሉም አካባቢዎች 250 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አሉ።