ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱ ግዙፍና ስትራቴጂክ ተቋማትን ይበልጥ ተወዳዳሪ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱ ግዙፍና ስትራቴጂክ ተቋማትን ይበልጥ ተወዳዳሪ አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱ ግዙፍና ስትራቴጂክ ተቋማትን ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግና የህብረተሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ ያስቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ ገለፁ።
የካፒታል ገበያ ለሀገሪቱ ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ ካፒታል ምንጭ የሚያስገኝና የፋይናንስ አማራጭን በማስፋት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋት የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ መመዝገቡን ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ባለአክሲዮኖች በሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አክስዮናቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ እንዲገዙና እንዲሸጡ የሚያስችል ነው።
በምዝገባ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ፣ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር)፣ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዲሁም የብሔራዊ ባንክና የሌሎች ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ እንደገለጹት፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ መዋቅሩን ማዘመን፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ተወዳዳሪነትና የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ነው።
የሀገሪቱ ግዙፍና ስትራቴጂክ ተቋማት ለበርካታ ዓመታት ሙሉ በሙሉ በእጅ ስር እንደነበሩ አስታውሰዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይህን አካሄድ በመቀየር ተቋማቱ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የህዝብ ተሳትፎ እንዲያድግ በር ከፍቷል ብለዋል።
በዚህም ኢትዮ-ቴሌኮም የባለቤትነት ይዞታውን ክፍት በማድረግ የመጀመሪያው የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆን በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በይፋ መመዝገቡን ተናግረዋል።
ምዝገባው ለወራት ሲካሄድ የቆየ የዝግጅት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ባለስልጣኑ ሂደቱ ግልፅነትና ዓለምአቀፍ አሰራር የተከተለ እንዲሁም የኢንቨስተሮችን መብት የሚያስጠብቅ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
የካፒታል ገበያ መመስረትና ማደግ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሀገሪቱ ግዙፍ ድርጅቶች ባለድርሻ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የካፒታል ገበያ ለሀገሪቱ ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ ካፒታል ምንጭ የሚያስገኝና የፋይናንስ አማራጭን በማስፋት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋት እንደሚደግፍም ተናግረዋል።
በሂደት ላይ ያሉ ተቋማትም የድርጅት አስተዳደራቸውን በማሻሻል ወደዚህ መድረክ እንዲመጡና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ምህዳር ይበልጥ እንዲሰፋና አማራጭ የካፒታል ምንጭ ለማግኘት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮ- ቴሌኮም ወደ ዘመናዊ የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ግብይት መግባት ለሥራቸው ታላቅ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም ባለአክሲዮኖች ወደ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሥርዓት መግባታቸውንና የንግድ አካውንት በመክፈት በአገናኝ አማካኝነት መገበያየት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ኢትዮ-ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻውን ለዜጎች መሸጡን ተከትሎ የባለአክሲዮኖችን መረጃ የመሰነድና የማደራጀት ሥራ በማከናወን በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አጸድቋል ብለዋል።
በዚህም አክሲዮን ከገዙ 47ሺህ 377 ባለአክሲዮኖች 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን አክሲዮኖችን በመሸጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል የ45 ሺህ ያህሉ ባለአክሲዮኖች መረጃ ተጣርቶ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን አክሲዮን በ3 ቢሊዮን ብር ለባለ አክሲዮንነት ብቁ ሆነው በመገበያያ ማዕቀፉ መካተታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የ96 በመቶ ባለአክሲዮኖች መረጃ ተጣርቶ የዲጂታል ባለቤትነት ማረጋገጫ ማግኘት መቻላቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።