በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ገለጸ።
የአእምሯዊ ንብረት ዘርፍ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ከሀገራዊ የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባና ጥበቃ ጋር ማቀናጀት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግዙፍ ኩባንያዎች ሃብት ከፍተኛው ድርሻ ወደ አእምሯዊ ንብረት እየተቀየረ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያም የአእምሯዊ ንብረት ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የፖሊሲ፣ የሕግና የዲጂታል የአእምሯዊ ንብረት አስተዳደር ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።
የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባ ሥርዓቱን በአስቻይ የአሰራር ምኅዳር ለሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ሕግና ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ለጥናትና ምርምር ሥራ መሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የንግድና ፈጠራ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
የአእምሯዊ ንብረት ዘርፍ የሕግ አማካሪ ኤልያስ ፍቅሩ፤ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ዓለምአቀፍ ፈጠራና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ወሳኝ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓት መጠናከር ፈጠራና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማች መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር የቦርድ አባል አርቲስት ጸደንያ ገብረማርቆስ፤ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሚደረግላቸው ምርቶች ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ አላቸው ብላለች።
ለዚህም የኪነ-ጥበብ ሥራ ቅጂና ተዛማጅ የሕግ ግንዛቤን በማጎልበት ጠንካራ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።