በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እየተመዘገቡና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙ የልማት ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እየተመዘገቡና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙ የልማት ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እየተመዘገቡና በየደረጃው የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙ የልማት ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
ብልጽግና ፓርቲ በድሬዳዋ በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ የታጀበ የማጠቃለያ የምረጡኝ ቅሰቀሳ አካሂዷል።
የብልፅግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በዋና ዋና የከተማው አደባባዮች በመዘዋወር ከፓርቲው ጎን መሆናቸውን ባስተላለፉት መልዕክቶች አረጋግጠዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በስታዲየም ለተሰበሰቡ አባላትና ደጋፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦችን በማስታረቅ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት አረጋግጠዋል ብለዋል።
በተለይም በለውጡ አመታት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በገጠርና በከተማ በተከናወኑ ልማቶች የሀገራችንን ከፍታ ያረጋገጡ አብነታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በተለይም በድሬዳዋ የተከናወኑት መሠረተ ልማቶችና የኮሪደር ልማት ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የአገልግሎት ማዕከልነቷን እያረጋገጡ መሆናቸውን አመላክተዋል።
እነዚህን ዘርፈ ብዙ ሰው ተኮር የልማት እና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በፓርቲው መሪነት ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
እየተመዘገቡና የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙትን ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ድምጻቸውን ለብልጽግና ፓርቲ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ እታገኘሁ ታደሰ እና ወጣት አነስ መሐመድ እንዳሉት፤ ባለፉት የለወጥ ዓመታት የድሬዳዋን ከፍታ እና የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል።