የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም መድረክ ጠንካራ የተወዳዳሪነት አቅም የገነባ ተቋም ነው - አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም መድረክ ጠንካራ የተወዳዳሪነት አቅም የገነባ ተቋም ነው - አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም መድረክ ጠንካራ የተወዳዳሪነት አቅም የገነባ ተቋም መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀናት በፊት የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በተለያዩ ሆነቶች በደማቅ መርሃ ግብር አክብሯል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ተቋማዊ ዕድገትን ማስቀጠል እያስቻሉት ነው።
አየር መንገዱ በገነባው የረጅም ዘመናት ዓለምአቀፍ ስምና ዝናም ከአሜሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጋር ጠንካራ የትብብር አጋርነት እንዳለው ገልጸዋል።
ለአብነትም በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ከቦይንግና ጂኢ-ኤሮስፔስ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ጥብቅ አጋርነት ያለው ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም የሚያስተሳስር አስደናቂና ግዙፍ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗንም አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዳዲስ የመንገደኛ አውሮፕላን፣ የበረራ መዳረሻ በማስፋትና በሀገር ውስጥ የአየር ማረፊያ መሠረተ ልማት ግንባታ አስደናቂ ሥራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባው አቅም ቀጣናዊ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በዓለም መድረክ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትን ጨምሮ በአስቸጋሪ ወቅቶች በአሜሪካና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የተገነባው ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ጠንካራ ትብብርና አጋርነት የክትባትና መድኃኒት ቁልፍ ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ ከፍተኛ ሚና እንዲወጣ ማስቻሉን አስታውሰዋል።
የአየር መንገዱ የወደፊት ዕቅድና የአቅም ግንባታ የትኩረት መስክ ለቀጣይ ስኬቱ ቁልፍ እንደሚሆኑም አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕድገት ጉዞ ላይ አሜሪካና የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎቿ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የልማትና የትብብር መስኮች እየተጠናከረና እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።