በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጓል
መቱ፣ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት በመሰራቱ የተሻለ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ።
በመቱ ከተማ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 48 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በክልሉ ከተሞች የሚከናወኑ የሕንጻዎችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ምቹ የመኖሪያና ማሕበራዊ አካባቢዎችን ለመፍጠር፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ቀልጣፋና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለማስፈን ያለሙ መሆናቸውም ተገልጿል።
በምረቃ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከተሞች በቂ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ፍትሐዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ከማስፈንና የማሕበረሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ በክልሉ በየጊዜው እየተገነቡ ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ኤጄርሶ በበኩላቸው፣ ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት 48 ፕሮጀክቶች መካከል የትምህርት ቤቶች ግንባታና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የመንገድ ዳር የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የንግድ መስሪያ ቦታ ሼዶች፣ የከተማ ግብርና ማዕከላት፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ እና የከተማ አስተዳደር ሕንጻም መመረቁን ተናግረዋል።
ከንቲባው ፕሮጀክቶቹ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመንና ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ፣ የሕብረተሰቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ከተማዋን ውብና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ የሚረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱራህማን ኢድሪስ እና አቶ ተስፋዬ ኮንቺ ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት የገባው የከተማ አስተዳደሩ ሕንጻ የከተማዋን ገጽታ የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ወይዘሮ ኑሪያ ሁሴን እና አቶ መሐመድጣሂር አባገሮ በበኩላቸው የተገነቡት ሼዶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ሠርተው የሚለወጡበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
የመንገድ ዳር የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆንና አደጋ እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ፣ የከተማዋን ውበት በመጨመር ለመኖሪያነት ምቹ አድርጓታል ብለዋል።