ቀጥታ፡

የከተማውን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ለንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ምቹ ለማድረግ ትከረት ተሰጥቷል

ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 18/2018  (ኢዜአ)፡- በወላይታ ሶዶ ከተማ የመንግስት አገልግሎትን በማዘመን  ከተማውን ለንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ምቹ  ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ  ወጪ ለሚያስገነባው የባለ 12 ወለል የቢሮ ሕንፃ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በወቅቱ እንደገለጹት የወላይታ ሶዶ ከተማ ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን ተከትሎ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን አስፈልጓል።

ግንባታው የተጀመረው የከተማ አስተዳደሩ የቢሮ ህንጻ ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ በመፍጠር የመንግስት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል ።

የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ከተማዋን ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት በቅንጅትና በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በከተማ አስተዳደሩ ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሚገነባው ዘመናዊ የቢሮ  ህንፃ  የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው ህንጻው ከተማዋን ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭና ተወዳዳሪ  ለማድረግ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፤

የቢሮ ህንጻው በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገነባ መሆኑን ጠቁመው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም