ቀጥታ፡

የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የተሻለች ሀገር የሚገነባ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

ጊምቢ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የተሻለች ሀገር የሚገነባ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቶቹ እንደተናገሩት፤ በምርጫው የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ፍላጎት መጪው ጊዜ ላይ በተግባር የሚያረጋግጥ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

ከዞኑ ወጣቶች መካከል የሆማ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ጉታማ ሁንዴሳ በሰጠው አስተያየት፤ የወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግና ሀብት እንዲያፈሩ በትኩረት የሚሠራ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቷል።

በምርጫው ዕለት ዲሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም፣ ለወጣቱ የተሻለ ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑንም ገልጿል።

ሌላው የቤጊ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ገመቹ ኦላና በበኩሉ፤ የወጣቶችን የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ገመቹ፤ የፓርቲዎቹ ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ወጣቱ ለሀገር የሚበጅ የተሻለ ሐሳብና ፖሊሲ ያለውን ለይቶ ለማወቅ መልካም ዕድል እንደሚፈጥር አስረድቷል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንዲከበር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጿል።

ወጣቱ የተሻለ ኑሮ እንዲመራ በትጋት የሚሠራን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ የሆማ ከተማ ነዋሪው ወጣት ክፍሉ አስፋው ነው።

በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ከሕዝቡ ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወጣት በመሆኑ፣ ወጣቱ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በፓርቲዎቹ እየቀረቡ ያሉትን የፖሊሲ አማራጮች በተገቢው መንገድ በመረዳት ድምፁን መስጠት እንዳለበት ጠቁሟል።

በመጨረሻም ወጣቶቹ፣ በወሰዱት የምርጫ ካርድ አማካኝነት ነገ የተሻለ ዕድገትና ተስፋ ያመጣል ለሚሉት ፓርቲ ድምፃቸውን በነፃነት በመስጠት፣ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም