በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶችን በማንቃትና በማስገንዘብ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው - የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶችን በማንቃትና በማስገንዘብ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው - የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶችን በማንቃትና በማስገንዘብ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ድምፅ መስጫ ቀን ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምዕራፎች በማካሄድ ከየካቲት 28 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎቹ በአካል በመገኘት የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ከ50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።
በጠቅላላ ምርጫውም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ በስፋት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።
በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሲቪል ማኅበራት እንዳሉት፤ ድምፅ መስጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች የመምረጥ መመረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮሴፍ አበራ፤ ሀገር አቀፍ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማጠናከሪያ ቁልፍ መሳሪያ ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫም ወጣቶችን በማንቃት፣ በማስገንዘብና የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ በማድረግ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጿል።
ከ32 ሺህ በላይ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራትና የፌዴሬሽኑ አባላትን በማንቃት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ25 ሚሊየን በላይ ወጣቶች የምርጫ ካርድ እንዲወሰዱ መደረጉን ተናግሯል።
በቀጣይም የምርጫ ሂደቱ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶችን ሚና በማላቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስቷል።
የፌዴሬሽኑ አባል ከተማ ባህሩ፤ ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው ሂደት ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መመረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
የፌዴሬሽኑን አባላት ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶችን በማስገንዘብ የወሰዱትን የምርጫ ካርድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉት የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ የፌዴሬሽኑ አባል ቢታንያ ዓለምሰገድ በበኩሏ፤ በተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች ወጣቶች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ በማድረግ በሂደቱ ንቁ ታሳታፊ እየተደረጉ ነው ብላለች።
በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ስለሺ ሳልስዑመር በበኩሉ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችን በማስገንዘብ ምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ተደርጓል ብሏል።
በድምፅ መስጫ ዕለቱም ወጣቶች የወሰዱትን የምርጫ ካርድ እንዲጠቀሙ የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።