ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን በታቀደለት ጊዜ ለማካሄድ ሁሉም ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን በታቀደለት ጊዜ ለማካሄድ ሁሉም ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን በታቀደለት ጊዜ ለማካሄድ ሁሉም ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ።
የምርጫው የጥሞና ጊዜ ከግንቦት 20 ቀን ጀምሮ በመሆኑ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረው ጥቂት ጊዜ ውስጥ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሥራቸውን እንዲያጠናቅቁም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ፣ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተደረጉ አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው እንዳሉት፤ ቦርዱ ምርጫውን በታቀደለት ጊዜ ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ ሁሉንም ዝግጅቶች አጠናቅቆ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ምዝገባን እንዲሁም ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም የምርጫ ቁሳቁሶችን የማደራጀትና ወደ ምርጫ ክልሎች የማድረስ ሥራ መከናወኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ ይሄንን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አብራርተዋል።
መራጩ ሕዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ 19 የክርክር መድረኮች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፉ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም ነፃ የአየር ሰዓት ድልድልን በተመለከተ 782 ነጥብ 5 ሰዓት የሬዲዮ፣ 520 ሰዓት የቴሌቪዥን እና 576 የጋዜጣ አምድ ለፓርቲዎች ተሰጥቷል ነው ያሉት።
ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት 64 የሚዲያ ተቋማት እና 1 ሺህ 814 ጋዜጠኞች የዘገባ እውቅና ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ቦርዱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆኑ አካላትን በመመደብ በሂደቱ ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን በገለልተኝነት ሲያስተናግድ መቆየቱንም ገልጸዋል።
የምርጫው የጥሞና ጊዜ ከግንቦት 20 ቀን ጀምሮ በመሆኑ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረው ጥቂት ጊዜ ውስጥ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሥራቸውን እንዲያጠናቅቁ ሰብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።
መራጮችም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በየምርጫ ጣቢያዎቻቸው በመገኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ድምፃቸውን እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።