ቀጥታ፡

በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ውጤታማነታቸውን የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ውጤታማነታቸውን የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የአርባ ምንጭ "ያላ አግሮ ኢንዱስትሪ"ን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።




ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በምረቃ መርሃግብሩ ላይ እንዳሉት፤ በክልሉ የልማት ጸጋዎችን ለይቶ እሴት ጨምሮ ለማምረት የኢንዱስትሪ ዘርፉን አቅም ማሳደግ ይገባል።

ለዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ እሴት ጨምረው ለገበያ እንዲያቀርቡና ለአርሶ አደሩም የግብይት አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ዛሬ ወደሥራ የገባው ያላ ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማበረታታት የሚሰራው ተግባር ውጤታማነት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ውጤታማነታቸውን የማረጋገጡ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ በክልሉ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብ የተቀናጀ ሥራ ከማከናወኑ ባለፈ የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል፣ የእንስሳት ጤናን የመጠበቅ እንዲሁም የእንስሳት መኖ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያላ የወተት አግሮ ኢንዱስትሪን ጨምሮ 142 አምራች ኢንተርፕራይዞች አሉ።



ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እሴት በመጨመርና ተኪ ምርቶችን በማምረት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት እያገዙ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ይህን በማጠናከር ለሀገር ዕድገት እና ለዜጎች ተጠቃሚነት የአምራች ኢንዱስትሪ ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉም አክለዋል።




የያላ አግሮ ኢንዱስትሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ እስራኤል፤ ኢንዱስትሪው በቀን 24 ሺህ ሊትር ጥራት ያለው ወተት ማቀነባበር እንደሚችል ገልጸዋል።

ለ150 ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ በእሴት ሰንሰለት ከ5 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።




ኢንዱስትሪው ፓስቸራይዝድ ወተት፣ ተፈጥሯዊ እርጎ፣ ቺዝ፣ ክሬም እና አይብ እንደሚያመርትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም