ቀጥታ፡

በዞኑ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቻችን ምላሽ እየሰጡ ነው - ነዋሪዎች

አምቦ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ መሠረተ ልማቶች የልማት ጥያቄዎቻቸውን የመለሱና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን የፈቱ መሆናቸውን የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ አምቦ ወረዳ በበጀት ዓመቱ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ማዕከል እና የባህል ፍርድ ቤቶች ተመርቀዋል።

እነዚህ የልማት ሥራዎች መጠናቀቃቸውና ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው የዞኑን ሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻልና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተመልክቷል።




የአምቦ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዴክስሳ ተረፈ እንደተናገሩት፤ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የጠጠር መንገድ ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የትራንስፖርት ችግር መፍታት ችሏል።

በአካባቢያችን ባለው ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመገንባቱ ምክንያት በክረምት ወቅት ወንዙን ተሻግረን ማሳችንን ለማረስ ባለመቻላችን በግብርና ሥራችን ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሮብን ቆይቷል፤ አሁን ግን መንገዱና ድልድዩ በመገንባታቸው ተደስተናል ብለዋል።

 

ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ሀዳ ስንቄ ወርቄ ቶለሳ በበኩላቸው ግንባታቸው ተጠናቅቆ በተመረቁ ፕሮጀክቶች መደሰታቸውን ገልጸው፤ ፕሮጀክቶቹ ማኅበራዊ መስተጋብርን ከማጠናከር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።

ተመርቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ክፍት የሆኑት መሠረተ ልማቶች 245 መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰረት ጉዲሳ ናቸው።




ፕሮጀክቶቹ በወረዳው ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ጭምር ሆነው የቆዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደጀኔ ተረፋ በፕሮጀክቶች ምረቃ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት ለሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል።

በዞኑ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በብዛትና በጥራት በመገንባት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።




በተለይም በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በግብርና እና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም