ቀጥታ፡

በክልሉ በክረምቱ ወራት ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሻይ ችግኝ ይለማል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ክረምት ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሻይ ችግኝ በኩታገጠም እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር አቶ ቻላቸው አዱኛ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በክልሉ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ለሻይ ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

ክልሉ ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የዝናብ መጠንና ለሻይ ተክል ተስማሚ የአፈር ዓይነት ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎም ልማቱ በስፋት እየተከናወነ የሚገኘው የዞኖቹን መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት መሰረት በማድረግ ሲሆን፤ በተለይም በጅማ፣ ኢሉአባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች ውስጥ በስፋት እየለማ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በዘንድሮው ዓመት ከተዘጋጀው 120 ሚሊዮን የሻይ ችግኝ ውስጥ፤ 42 ሚሊዮኑን በ3 ሺህ 168 ሄክታር መሬት ላይ በኩታገጠም ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።

ለዚህም እንዲረዳ የመሬት ልየታ ተካሂዶ በክላስተር የተደራጀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የጉድጓድ ቁፋሮ እና የሻይ ችግኝ ተከላ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግም የተሻሻሉ ዝርያዎች የሚባዙባቸው የሻይ ችግኝ ጣቢያዎች በመንግስትና በአርሶ አደሮች ደረጃ ለተከላ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በዘንድሮው የልማት ስራ 1 ሺህ 250 አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የሻይ ተክል ችግኞችን በኩታገጠም አሰራር ዘዴ ለመትከል ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት በክልሉ በአጠቃላይ 2 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በሻይ ተክል መሸፈኑን ጠቁመው፤ ከ1 ሺህ 200 በላይ አርሶ አደሮችም እየተሳተፉበት ይገኛል ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ ለሚያመርተው የሻይ ምርት አስተማማኝ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

በክልሉ ምዕራብ አካባቢዎች ባለው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት የመሬት አሲዳማነት ይከሰታል።

የሻይ ተክል ደግሞ ይህንን የአፈር አሲዳማነት ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል በመሆኑ፣ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅና የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራበት ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ የሻይ ልማት አሲዳማ መሬትን የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት መሰል የአፈር ችግር ባለባቸው በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ልማቱን ለማስፋፋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ቻላቸው አዱኛ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም