ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የሕዝብን እርካታ የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አጋርፋ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የሕዝብን እርካታ የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ መንግሥቱ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።

በባሌ ዞን የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ የአጋርፋ ወረዳ አስተዳደር እና የዞኑ የገንዘብ ጽሕፈት ቤት ሕንጻዎችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ539 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 በምረቃው ወቅት መንግሥቱ በቀለ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የወቅቱ ቁልፍ ጉዳይ ነው።


 

 የተገነቡት ሕንጻዎች ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ፤ ኅብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኝ ያግዛሉ ብለዋል።

 የመንግሥት ጥንካሬ የሚለካው ከሕዝቡ ጋር ባለው ቁርኝትና መስተጋብር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የጠንካራ መንግሥት መገለጫ እንደሆነ አክለዋል።

 የክልሉ መንግሥት ፍትሐዊና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለሕዝቡ ለማድረስ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልና አሁን የተመረቁት ፕሮጀክቶችም የዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፤ አዲሶቹ ሕንጻዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የመኪና ማቆሚያዎችና የተሟሉ የቢሮ ዕቃዎች ያሏቸው በመሆኑ አገልግሎቱን የተቀናጀና የተሳለጠ ያደርጉታል ብለዋል።


 

የአገልግሎት አሰጣጡ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ከሕንጻ ግንባታው ጎን ለጎን ለሰው ኃይል ሥልጠናና ልማት ሰፊ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

 በዞኑ በአጠቃላይ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ከ1 ሺህ 700 በላይ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው እየተመረቁ መሆኑን ገልጸዋል።

 በቀጣይም ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ሥራዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

 የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ መሠረተ ልማቶች የመንግሥት አገልግሎቶችን በቅርበትና ያለ እንግልት ለማግኘት ትልቅ እገዛ እንደሚደርጉላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም