ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ተመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ተመዘገበ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮ-ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻ የገዙ ባለአክሲዮኖች ያላቸውን አክሲዮን ማስተዳደር የሚችሉበትና በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ መመዝገቡን ገለጸ፡፡
በምዝገባ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ፣ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል፣የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዲሁም የብሔራዊ ባንክና የሌሎች ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ እንደገለጹት፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ መዋቅሩን ማዘመን፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ተወዳዳሪነትና የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ነው።
ኢትዮ-ቴሌኮም የባለቤትነት ይዞታውን በከፊል ለሽያጭ ክፍት በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህ ተግባር የፋይናንስ አካታችነትን የሚያሳድግ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የካፒታል ገበያ መመስረትና ማደግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሀገሪቱ ግዙፍ ድርጅቶች ባለድርሻ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
አክለውም የካፒታል ገበያ የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር በመሆኑ ሁሉም ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል በበኩላቸው፤ የኢትዮ- ቴሌኮም ወደ ዘመናዊ የሰነደ ሙዓለንዋይ ግብይት መግባት ለሥራቸው ታላቅ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም ባለአክሲዮኖች ወደ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሥርዓት መግባታቸውንና የንግድ አካውንት በመክፈት በአገናኞች አማካኝነት መገበያየት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዳሉት፤ ኢትዮ-ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻውን ለዜጎች መሸጡን ተከትሎ የባለአክሲዮኖችን መረጃ የመሰነድና የማደራጀት ሥራ በማከናወን በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አጸድቋል።
በዚህም አክሲዮን ከገዙ 47 ሺህ 377 ባለአክሲዮኖች 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን አክሲዮኖችን በመሸጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል የ45 ሺህ ያህሉ ባለአክሲዮኖች መረጃ ተጣርቶ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን አክሲዮን በ3 ቢሊዮን ብር ለባለአክሲዮንነት ብቁ ሆነው በመገበያያ ማዕቀፉ ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የ96 በመቶ ባለአክሲዮኖች መረጃ ተጣርቶ የዲጂታል ባለቤትነት ማረጋገጫ ማግኘት መቻላቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።