በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በስፋት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በስፋት ተዘጋጅተዋል
አዳማ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ ዘይቱን፣ ሎሚ፣ አፕል፣ ማንጎ፣ ግሽጣና ቴምር ይገኙበታል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሐመድሳኒ አሚን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ ይገኛሉ።
የዚሁ አካል የሆነውን የሙዝ ልማት ይበልጥ ለማሳካትና ምርጥ የሙዝ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ፣ ባቱን ጨምሮ ከተለያዩ የክልሉ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሙዝ ልማት የተሸፈነ ሲሆን፤ ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ60 ሚሊዮን በላይ የሙዝ ችግኞች በምርምር ማዕከላትና በአርሶ አደሩ ማሳዎች ላይ እንዲባዙ ተደርጎ ለተከላ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
የሙዝ ልማቱን ስኬታማ ለማድረግ ከክረምት ወቅት ባለፈ፤ በተለያዩ የክልሉ ዞኖች የበጋ መስኖ ልማት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ልማቱን በማስፋፋት ረገድ ከዚህ ቀደም የሙዝ ምርት በማይታወቅበት በምሥራቅ ሸዋ ዞንና በሌሎች የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ጭምር በስፋት እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
የሙዝ ልማቱ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ፤ አማራጭ የገቢ ምንጭን ለማስፋትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ወሳኝ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ለፓፓያ ልማትም 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፤ እነዚህን ችግኞች ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት።
በተጨማሪም በክልሉ የፍራፍሬ ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት የአቮካዶ፣ የብርቱካን፣ የዘይቱን፣ የሎሚ፣ የአፕል፣ የማንጎ፣ የግሽጣና የቴምር ችግኞችን በጥራት የማዘጋጀት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።