7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን በተግባር የምናሳይበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን በተግባር የምናሳይበት ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ለዓለም ማህበረሰብ በተግባር የምናሳይበት ወሳኝ መድረክ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ብልፅግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የምርጫ ቅስቀሳ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ከማለዳ ጀምሮ በተካሄደው መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ከንቲባና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል አዳነች አቤቤ እና ምክትል ከንቲባና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ጃንጥራር ዓባይ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ምርጫ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ለዓለም ህዝብ በተግባር የሚያሳዩበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሀ ግብሩ ፓርቲውን ከመደገፍ ባለፈ ኢትዮጵያውያን መንግስትን በምርጫ በህዝብ ይሁንታ ማጽናት የሚችሉ ብርቱ ህዝቦች መሆናችንን ለአለም የምንገልጽበት ነው ብለዋል።
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚጸናበት ህዝብ እውነተኛ የስልጣን ባለቤት መሆኑን የሚያስመሰክርበት መሆኑን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ስልጣን ከህዝብ ይሁንታ ውጭ ሊታሰብ እንደማይገባ አዲስ ምእራፍ የሚከፈት መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርጫው ሂደት እንዳይሳካ በባንዳነት ተግባር የተሰለፉ ቢኖሩም ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁጥር የመራጭነት ካርድ በመውሰድ የጠላትን ከንቱ ፍላጎት ማክሸፋቸውን አንስተዋል።
ብልፅግና የገባውን ቃል በተግባር የፈጸመ ፓርቲ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የአዲስ አበባ የዕድገት ደረጃም ብልፅግና ፓርቲን ሀገር የመለወጥ ርዕይ በይፋ የገለጠ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ለተመዘገቡ አንፀባራቂ የልማት ስኬቶችም ነዋሪ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን በመጥቀስ፤ የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎና ድጋፍም ዕውቅና እና ምስጋና የሚቸረው መሆኑን አንስተዋል።
ይህም የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የብልፅግና መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ይሁንታን ካገኘ የገባውን ቃል በእጥፍ በመፈጸም የተሟላ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደሚተጋ አረጋግጠዋል።
ህልማችን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ማውጣት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህንን በመገንዘብ ድምጻችሁን ለብልጽግና ስጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።