ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድን በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍፃሜ መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድንን ዛሬ ያገናኛል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሲዳማ ቡና በሩብ ፍጻሜው ነገሌ አርሲን 2 ለ 1 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ ገብቷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ቤንጂ ማጂ ቡናን 2 ለ 0 በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ነው። ኢትዮጵያ መድን የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባቤት መሆኑ ይታወቃል።

ቡድኖቹ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን አንድ ጊዜ ድል ሲቀናው በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

በ30ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን በሳሙኤል ሳሊሶ ግብ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።

ጨዋታው ሲዳማ ቡና ሁለት ዋንጫ ለማንሳት፣ ኢትዮጵያ መድን ዓመቱን በዋንጫ ለማጠናቀቅ በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ ወሳኝ የሚባል ነው።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የጨዋታው አሸናፊ በፍጻሜው ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ይገናኛል።

ትናንት በተደረገ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መቀሌ 70 እንደርታን በመለያ ምት በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።

በተያያዘም የዛሬው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ መርሐ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም በኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ቅድመ ዝግጅት ምክንያት የቦታ ለውጥ ማድረግ በማስፈለጉ ጨዋታው በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም