ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ጉዞ የሚሳካው በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ጥረት ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ጉዞ የሚሳካው በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ጥረት ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ጉዞ የሚሳካው በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ጥረት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።
ብልፅግና ፓርቲ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ሲያካሂድ የቆየውን የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ እና ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተገኘበት በዚህ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲው እጩዎች እንዲሁም በርካታ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ ብልፅግና ፓርቲ በተግባራዊ እቅዶቹ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የወደፊቱን የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ለማሳካት እየተጋ ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ስብራትን እና ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ብልፅግና ማለት ለእያንዳንዱ ዜጋ እኩልነት፣ ፍትህ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህ ታላቅ ሀሳብ ከግቡ ሊደርስ የሚችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሴራና መከፋፈል እድገትን እንደሚያፈርስ ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተሰበሰብነው ሀገርን በጋራ ለመገንባት ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
የፓርቲው እቅዶችና የልማት ስራዎች በተግባር መሬት እየረገጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች የልማት መስኮች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘላቂ ስራዎችን በተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ሕብረ ብሄራዊ አንድነታችንን፣ ሰላማችንንና የመሰረተ-ልማት ግንባታችንን በማጠናከር የጀመርነውን የልማት ጉዞ በስፋትና በላቀ ደረጃ እንቀጥላለን ብለዋል።
ወጣቶችና ሴቶች በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፍ የላቀ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት እንዲኖራቸው ሰፊ እድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ወጣቶች እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በመጠቀም ሀገራቸውን በፅናት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እያሸጋገሯት እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በምርጫ ሂደት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም ዜጋ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት የጠቆሙት አቶ አረጋ፤ የፖለቲካ ስልጣን ከጦርነት ሳይሆን ከህዝብ ድምፅ ብቻ እንደሚገኝ በተግባር ማሳየት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸውና በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ተከፋፍለው እንደማያውቁ አስታውሰው፤ ማናቸውንም የውስጥ ልዩነቶች በጦር መሣሪያና በብረት ሳይሆን በሰለጠነ የውይይትና የሰላም መንገድ ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራና በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሁላችንም ጥረትና ስኬት የኢትዮጵያ ስኬት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄያችንም የነፃነታችንና የኢኮኖሚ ነፃነታችን ዋስትና በመሆኑ ለስኬቱ መትጋት አለብን ብለዋል።