ቀጥታ፡

በፓርቲው መሪነት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ስኬታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ግንቦት 18/2018(ኢዜአ)፦በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ስኬታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ክልል አቀፍ የብልጽግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በፓርቲው አመራርነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስኬታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በሲዳማ ክልልም ለዜጎች መሰረተ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎች በመንገድ ልማት፣በንፁህ መጠጥ ውሃ፣በኤሌክትሪክ፣ በጤናና በትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በገጠር የማህበረሰቡን ትስስርና የንግድ እንቅስቃሴው የሚያሳድጉ አዳዲስ መንገዶች ተገንብተዋል ያሉት አቶ ደስታ፥ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ እንዲሁም በርካታ የመስኖ አውታሮችን በመዘርጋት የአርሶ አደሩን ጤናና ምርታማነት ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የተጀመሩ እና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጹን ለፓርቲው እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ብልጽግና ኢትዮጵያን ከተረጂነት አውጥቶ ስንዴ ወደ መላክ ያሸጋገረ የመቻልና የአይበገሬነት ተምሳሌት የሆነ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

በፓርቲው መሪነት በኢንዱስትሪ፣በግብርና፣በሌማት ትሩፋትና ሌሎች አካታች የልማት ሥራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

ፓርቲው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ የሆኑ የልማት ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አውስተው፣ በሲዳማ ክልልም ሀዋሳን ጨምሮ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ ምርቱን ወደገበያ ወስዶ በመሸጥ በተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤት መገኘቱንም አመልክተዋል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፥ ፓርቲው ለሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ትኩረት የሚሰጥ፣ያቀደውን በተግባር የሚፈጽም እና የዛሬውንና የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርጎ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፓርቲው መሪነት በማህበራዊ ፣በኢኮኖሚያዊ ፣በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲ መስኮች ለማከናወን የታቀዱትን በስኬት ማከናወን እንደተቻለም ገልፀዋል፡፡

የፓርቲው የቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ በሲዳማ ባህላዊ የቄጣላ ሥነስርዓትና ሌሎች ትዕይንቶች ታጅቦ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም