ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ጉዞና ትንሳኤ እውን እያደረገ ነው - የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ጉዞና ትንሳኤ እውን እያደረገ ነው - የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ) ፦ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ጉዞና ትንሳኤ እውን እያደረገ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር በሚል መሪ ሀሳብ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያና ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተገኘበት የድጋፍ ሰልፍና በዚህ የሕዝብ ድጋፍና የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲው እጩዎች እንዲሁም በርካታ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የፓርቲው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ብልፅግና በተግባር የተፈተነ፣ የሚታይና የሚዳሰስ ውጤት ያመጣ የልማት ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ሀገር ከፓርቲ በላይ ናት የሚለውን መርህ በተግባር ማሳየቱን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፣ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የባሕር ዳር ሕዝብ ያሳየውን የዴሞክራሲ ምርጫ ሙሉ በሙሉ አክብሮ በአካባቢው ታላላቅ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ለአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗን ያመለከቱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ባለፉት ዘመናት ፊታቸውን አዙረው የነበሩ ዓለም አቀፍ አካላት ማዕቀቦቻቸውን በማንሳትና ቃል ኪዳናቸውን በማደስ ወደ ሀገሪቱ እየተመለሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የፓርቲውን ሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥና ስኬቶች በማንሳትም ግብርናን በማዘመን ሀገሪቱ በበጋ ስንዴና በሩዝ ምርት ራሷን ችላለች ብለዋል።
የኢኮኖሚ መሪነቱን እየያዘ የመጣው የኢንዱስትሪ ዘርፍ መነቃቃት እያሳየ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከፍተኛ እመርታ አስመዝግቧል ነው ያሉት።
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማሳካት አዳዲሶችን መጀመሩን ገልጸው፥ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ የማዳበሪያና የጋዝ ምርት ዝግጅቶች እንዲሁም የኒውክሌር ኃይልን ለመጠቀም የተጀመረው ጉዞ የሀገርን አቅም እያሳዩ ነው ብለዋል።
በትምህርት ለትውልድ መርሐ ግብር ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል፣ የተማሪዎች ምገባን የማስፋፋት፣ የፈተና ሥርዓትን የማሻሻልና መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት የማምረት ተግባራት በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከመሽኮርመም ወጥቶ ደፋርና ልክኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዘመናት ሲንከባለል የኖረውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በብልፅግና በሳል ውሳኔና ቆራጥ እርምጃ መጠናቀቁንና የኮይሻ ግድብ ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል ብሎ ጥቅሟን መሠረት አድርጎ በፅናት እየሞገተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታትም መንግሥት ዘላቂ የኢኮኖሚ መፍትሔ እየወሰደ ሲሆን ለዚህም ዋናው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ትንሣኤና መበልጸግ እውን ለማድረግ፣ የጥረት፣ የአንድነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት የሆነውን የስንዴ ነዶ ምልክት በመምረጥ ሕዝቡ ለብልፅግና ፓርቲ ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።