ቀጥታ፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል- ሸማቾች

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በየአካባቢው መስፋፋታቸው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ይገኛሉ።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፥ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያችን በመጀመሩ የግብይት ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ምቹ አድርጎታል።

ከአስተያየት ሰጪ ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ገነት አድማሱ፤ገበያው በአቅራቢያችን በመከፈቱ የፍጆታ እቃዎችን በቀላሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት አስችሎናል ብለዋል።

ይህ አይነቱ ገበያ መኖሩ ለነዋሪዎች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎትን ከማግኘት ባለፈ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ወደ ገበያው ሲመጡ የመጀመሪያ ቀናቸው እንደሆነ የነገሩን ወይዘሮ ጸጋ አዱሽ በበኩላቸው፤ በቅዳሜና እና እሁድ ገበያዎች የአትክልትና ፍራፍሬ በብዛት ከመቅረቡም ባሻገር ሰፊ አማራጮች የሚገኙበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የጥራጥሬ እህሎች ሱቅ ላይ ከሚሸጡ እቃዎች የዋጋ ልዩነት ያለው በመሆኑ በገበያው ደስተኛ መሆናቸውንና በቀጣይም በቋሚነት እንደሚመጡ ተናግረዋል።

የቅዳሜና እሁደ ገበያዎች በየአካባቢው መኖሩ ለአቅመ ደካሞች እና ረዥም መንገድ ተጉዘው መገበያየት ለማይችሉ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልጸው፤ገበያው ላይ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያገኝ የገለጸችው ደግሞ ማአዛነሽ መለሰ ናቸው።

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ነጋዴዎች በበኩላቸው ፤ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

እየሩሳሌም ሐብቶም፤ የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ነዋሪዎች ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ይህን ፍላጎት ለማሟላት ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጠነ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ሌላኛዋ ነጋዴ ቤተልሔም አዱኛ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የዋጋ ንረትን በመቀነስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት መጀመሩን ገልጸው፤ ከመደበኛ ሱቆች ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ሸማቾች በቀላሉ በአቅራቢያቸው መገብየት የሚያስችሉ በሁሉም አካባቢዎች 250 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አሉ።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም