ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 18/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ቅስቀሳ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ከማለዳ ጀምሮ በተካሄደው መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አዳነች አቤቤ፣ምክትል ከንቲባ እና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ጃንጥራር አባይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ቡዜና አልከድር፣ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች እና የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለአለም በምርጫ ብቻ እንደሚያምኑ እና ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት እንደሚችሉ የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ዋናው ግብ መሆኑንም ገልጸዋል።
ምርጫው እንዳይሳካ በባንዳነት የሚያገለግሉ መኖራቸውን ገልጸው ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ጠላትን ማሳፈሩን ተናግረዋል።
ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ የተግባር ፓርቲ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ አሁን የደረሰችበት ደረጃ ብልጽግና ፓርቲ ያለውን ራእይ አፍ አውጥቶ የሚመሰክር መሆኑን ተናግረዋል።
ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ምንም የተከናወነ ስራ አለመኖሩን ገልጸው ይህም እውቅና የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የተከናወኑ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እና የብልጽግና መሰረት የጣሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም የህዝብ ይሁንታ ካገኘ የገባውን ቃል በእጥፍ እንደሚተገብር ገልጸዋል።
ህልማችን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ማውጣት ነው ያሉት ከንቲባዋ ይህንን በመገንዘብ ድምጻችሁን ለብልጽግና ስጡ ስጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።