ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ማዕቀፍ የዲፕሎማሲ መርህ መሳካት የሚችል የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ፍትሕዊ የባሕር  በር ባለቤትነት ጥያቄም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር ከምታደርገው ጥረት ጋር ተለይቶ የሚታይ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያዊያን የጋራ መስዋዕትነት በተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ስትራቴጂ መነሻነት አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማፋጠን ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን በመጠቀም በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ቁርኝት ተፈጥሮን ከመልክዓ ምድራዊ ታሪካዊነትን ከሕጋዊነት ያሰናሰለ መሆኑን አስረድተው፤ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንድታጣ የተደረገበት በሴራና ተንኮል የተሸረበ አካሄድም የሚያስቆጭና ኢትዮጵያን ደካማ ለማድረግ ካለ እሳቤ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ፀጋዋን በመጠቀም ዕድገትን ካረጋገጠች ስጋታችን ትሆናለች የሚለው ስሌትም የታሪካዊ ጠላቶች ኋላቀርና የተሳሳተ ደምዳሜ ነው ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ መሠረተ ያለው፣ ተፈጥሯዊና መልክዓ ምድራዊ እውነታ ያለው ሕጋዊና ፍትሐዊነትን አሰናስሎ የያዘ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ቦሊቪያና ፔሩ፣ ብራዚልና ፓራጓይ፤ በአፍሪካ የማሊ፣ ሴኔጋልና ኮትዲቯር የተጠቀሙባቸውን የጋራ መፍትሔዎች በተሞክሮነት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ማዕቀፍ የዲፕሎማሲ መርህ መሳካት የሚችል የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ፍትሕዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሳካት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ላላት ሀገር የቅንጦት ሳይሆን የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን የሚያስከብር ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ለወደብና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በየዓመቱ የምታወጣው ከፍተኛ ሃብት ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትና በጠቅላላው የዕድገት ጉዞ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም