በምግብና መጠጥ ማቀነባበር የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ህብረተሰቡ በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምርቶችን እንዲያገኝ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምግብና መጠጥ ማቀነባበር የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ህብረተሰቡ በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምርቶችን እንዲያገኝ እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦ በግብርና ምርት የምግብና መጠጥ ማቀነባበር የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ህብረተሰቡ በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምርቶችን እንዲያገኝ እያደረጉ መሆናቸውን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ከቴክኖ-ሰርቭ ጋር በመተባበር የበለፀገ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት የገበያ ትስስር ፎረም በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደበበ ወርቁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በምግብ ዘርፍ የስንዴና የማሽላ ዱቄት የጨውና የዘይት ምርቶች አስገዳጅ ደረጃ ወጥቶላቸዋል።
በዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎች የበለፀገ የምግብ ምርት ዝግጅት ሰርተፊኬት በመውሰድ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡበትን የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ ምርት አምራቾችም በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምርቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በንጥረ ነገር በለፀገ የምግብ ምርታማነት አቅም ጤናማና አምራች ዜጋን በማፍራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አንስተዋል።
በቀጣይም በበለፀገ የምግብ ምርት ማቀነባበር ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ በማድረግ የምርት ጥራትና አቅማቸውን እንዲያሳደጉ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በቴክኖ ሰርቭ ተቋም የሚለር ፎር ኒውትሬሽን ፕሮግራም ማናጀር ገረመው ጣሰው በበኩላቸው፤ አምራቾች የተሳለጠ የምግብ ማበልፀግ ሥራ እንዲያከናውኑ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በበለፀገ የምግብ ማቀነባበርና ዝግጅት ለተሰማሩ ድርጅቶች የሚያደርገውን አተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዋኬኒ ምግብ ፋብሪካ ፕሮዳክሽን ማናጀር አማኑዔል ታደሰ፤ መንግስት ለፋብሪካዎች የሰጠው ልዩ ትኩረት ምርቶቻችንን በጥራትና በስፋት ተደራሽ እንድናደርግ አስችሎናል ብለዋል።
ሌላኛው የዲና ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሽያጭና ስርጭት ሥራ አስኪያጅ እንየው ጫኔ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ ታምርትን ጨምሮ መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርገው ድጋፍ እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።