በክልሉ የአርብቶ አደሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአርብቶ አደሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል
ሰመራ፣ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በአርብቶ አደሩ አካባቢ ለንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በተሰጠው ትኩረት ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር ገለጹ ።
በክልሉ አፍዴራና ቢዱ ወረዳዎች ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር በወቅቱ እንደገለፁት በአርብቶ አደሩ አካባቢ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል ።
በዚህም አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በወረዳዎቹ ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት የውሀ ተቋማትም የጥረቱ አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
አካባቢው በረሀማ በመሆኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ በቀዳሚነት አሰፈላጊና ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው ከተለያዮ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ አህመድ ሻሚ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳዎቹ ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት የንፁህ መጠጥ ውሀ ተቋማት በጸሀይ ሀይል የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ተቋማቱ በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክትና በወርልድ ቪዥን የገንዘብ ድጋፍ በትብብር የተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በአፍዴራ ወረዳ ነማ ጉቢና ቀበሌና በቢዱ ወረዳ ቢዱ ሶዶምታ ቀበሌ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የንፁህ መጠጥ ውሀ ተቋማት ከ30 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
የአፍዴራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲራጅ መሀመድ የውሀ ተቋሙ መገንባት የህብረተሰቡን ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አስታውቀዋል።